Home Interviews "የኢሳይያስ ፣ዲክታቶርያል፣ መንግሥት... (The Reporter, interview with ECP Chair person)
"የኢሳይያስ ፣ዲክታቶርያል፣ መንግሥት... (The Reporter, interview with ECP Chair person) PDF Print E-mail
Written by The Reporter   
Monday, 10 August 2009 18:32
"የኢሳይያስ ፣ዲክታቶርያል፣ መንግሥት... E-mail
Sunday, 02 August 2009

Image"የኢሳይያስ ፣ዲክታቶርያል፣ መንግሥት እንዲያውም ኃይለኛ እና የማይነቃነቅ [ሆኗል]"

አቶ ኅሩይ ተድላ ባይሩ የሰልፊ ጉባኤ ኤርትራ (የኤርትራ ኮንግሬስ ፓርቲ) ሊቀመንበር ናቸው፡፡ አባታቸው "አንድነት ወይ ሞት" በሚል ሲንቀሳቀሱ የነበሩና ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በፌዴሬሽን ስትጠቃለልም የኤርትራ መሪ ነበሩ፡፡

13 የፖለቲካ ፓርቲዎች አባል የሆኑበት የኤርትራ ዲሞክራሲያዊ ኪዳን (ጥምረት) በቅርቡ "የኤርትራ ብሔራዊ ኮንፍረንስ" ለማካሄድ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ጥምረቱ ኮንፍረንሱን አስመልክቶ የቅድመ ዝግጅት ዓውደ ጥናት አካሂዷል፡፡ አቶ ኅሩይ ስብሰባውን በታዛቢነት ተሳትፈዋል፡፡
ስለ ተቃዋሚዎቹ እንቅስቃሴ፣ ኮንፍረንሱ ይዘት፣ ስለኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭትና ኤርትራ ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የማነ ናግሽ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፈው ዓመት የኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ኪዳን ጉባኤ ሲያካሂድ የእርስዎ ፓርቲ ታዛቢ ሆኖ ነበር የተሳተፈው፡፡ አሁንም በተካሄደው ስብሰባ ታዛቢ ሆኖ ነው የተሳተፈው፡፡ ለምን?

አቶ ኅሩይ፡-
"ኪዳን" የተባለው ጃንጥላ የእኛን ፓርቲ አልቀበልም ካለ አራት ዓመቱ ነው፡፡ በየዓመቱ አባልነት እንጠይቃለን፤ በተለያዩ ምክንያቶች አንቀበልም ይላል፡፡ አሁንም እንደተለመደው አባል እንድንሆን ጠይቀን ነበር፡፡ ኮንግረሳችሁን አቋቁሙ ተብለናል፡፡ ሕጉ ግን አንድ ዓመት ነው የሚለው፡፡ ሶስት ወር ይቀራችኋል፣ አንቀበልም አሉን፡፡ አንዳንዱ ሰው ተደናግጧል፡፡ ምንድን ነው ነገሩ እያለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሦስት ወር ስለቀራችሁ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለ?

አቶ ኅሩይ፡-
ሌላ ምክንያት ባላቀርብ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም ግርግር ወይም የተለያዩ ግምቶች እንዳይፍጥር እነሱ ባሉት ብቻ ብንሄድ ይሻላል፡፡ እነሱ የሚሉት ጉባኤያችሁን አካሂዱ ነው፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ጉባኤ ይዘጋጅ ብለዋል፡፡ ውሳኔ የተሰጠ ቀን መጀመር ነበረብን ማለት ነው፡፡ ለጉባኤ ዝግጅት ቢያንስ ሦስት ወር ያስፈልጋል፡፡ ሦስት ወር ወስደን ጉባኤያችንን እነርሱ ራሳቸው በተሳተፉበት አካሂደናል፡፡ ሦስት ወር የዝግጅት ጊዜ መባል ነበረበት፡፡ ይህንን ባለማድረጋቸው የሕግ ስህተት ፈጽመዋል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ያቀረቡት ምክንያት ሁለት ማዕከላዊ ሽማግሌዎች አልመሰከሩም ነው፡፡ ሕጉ እንደዚህ አይልም፡፡ ሕጉ የሚለው ሁለት የኪዳን አባሎች ጉባኤ ሲደረግ መጥተው መታዘብ አለባቸው ነው፡፡ በሁለቱም ተሳስተዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ስለሚሰበሰቡ በተዘዋወሪ ደብዳቤ መልክ ቢያርሟቸው ይሻላል፡፡ ሁላችንም አብረን አስመራ ያለውን አምባገነን ብንገጥም ይመረጣል፡፡ ትንንሽ ምክንያቶን አምጥቶ ታጋዮችን ከትግሉ ከማስወገድ፣ አብረን እንታገል ማለቱ ይሻል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የኤርትራ ተቃዋሚ ድርጅቶች ጉባኤ አካሄዱ የሚል ዜና ተደጋግሞ ይሰማል፡፡ በመሃሉ ደግሞ ተጣልተዋል ይባላል፡፡ ከዚህ አንፃር ኮንፍረንሱ ይካሄዳል? ምን አዲስ ነገር ይጠበቃል?

አቶ ኅሩይ፡
- ትልቁ ተስፋችን ይካሄዳል የሚል ነው፡፡ ነገር ግን በምኞታችንና በኮንፍረንሱ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ አስተባባሪ ኮሚቴ ሽማግሌ በኪዳን የተመረጠ ከሆነ የኪዳን ጉባኤ ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡ የሕዝብ ጉባኤ ነው ከተባለ ሁሉም አካላት አዘጋጅ ኮሚቴው ውስጥ መኖር አለባቸው፡፡ እነሱ በሌሉበት የኪዳን ጉባኤ ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡ ምክንያቱም አዘጋጅ ኮሚቴው የኪዳን አስፈፃሚ ኮሚቴ ይመርጣል ነው የተባለው፡፡ ይህ ስለተባለ፣ በውጭ የሚቀመጡ ኤርትራውያን ይሄማ እንደገና የኪዳን ስብሰባ ሊሆን ነው እያሉ አዝነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሕዝባዊ ጉባዔ ሲባል ምን ማለት ነው? የኤርትራ ሕዝብ በምን መልኩ ነው በኮንፍረንሱ ተሳታፊ የሚሆነው?

አቶ ኅሩይ፡-
ውጭ አገር ያለው፣ በተለይ ሱዳን ውስጥ የሚገኘው ግምት ውስጥ ያስገባን ከሆነ ከግማሽ የኤርትራ ሕዝብ አያንስም፡፡ በጣም ሰፊ ነው፡፡ እነ"ህ ኤርትራውያን በተለያዩ አካላት መገለፅ ይችላሉ፡፡ ስደተኞች አንድ አካል ናቸው እና የራሳቸው ወኪሎች የግድ መምረጥ አለባቸው፡፡ በአውስትራሊያ፣ በአፍሪካ፣ በመካከለኛ ምሥራቅ ያሉት የራሳቸው ተወካዮች መርጠው ካልላኩ፣ ጉባኤ ነው ብሎ ለመጥራት ያዳግታል፡፡ ኪዳን ውስጥ የሌሉ የፖለቲካ ድርጅቶችም አሉ፡፡ እነሱ ካልተሳተፉ አጠቃላይና አሳታፊ የሆነ ብሔራዊ ኮንፍረንስ ተካሄደ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምሁራንም እንዲሁም ጠቃሚ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ካልመጡ፣ የጉባኤው አዘጋጆች፣ የኪዳን መሪዎች ሰውን መርጠው ሊያዘጋጁት ማለት ነው፡፡ እነዚህ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎች ካልተወሰዱ ብሔራዊ ኮንፍረንስ ተካሄደ ማለት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ጉባኤ የሚካሄድበት ቦታና ጊዜ ተወስኗል?

አቶ ኅሩይ፡-
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተብሏል፡፡ ይህም ራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ከአቶ ኢሳያስ ጋር ቀጠሮ የተደረገ ይመስላል፡፡ አስቀድሞ ቢደረግ ትግሉ እየጠነከረ ይሄድ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር የተስተካከለ ይመስል በአንድ ዓመት ይሁንልን ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ የትግሉ ጊዜ ይራዘማል፡፡ በደንብ አይደራጅም፡፡ ኮንፍረንስ የፈለግነው በአጭር ጊዜ ተዘጋጅቶ የአሥመራውን አምባገነን ከኤርትራ መሬት ማስለቀቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢሳይያስ ጋር ቀጠሮ ያለ ይመስል ሲሉ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የኢሳይያስ መንግሥት ይወገዳል የሚል ግምት አለዎት?

አቶ ኅሩይ፡-
አይደለም፡፡ አንድ ዓመት ከመሙላቱ በፊት በአጭር ጊዜ ቢዘጋጅ ይሻላል ለማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባካሄዳችኋቸው ጉባኤዎች ሁሉ የኢሳይያስ መንግሥት ከሕዝብ ተነጥሏል፣ ሊወድቅ ተቃርቧል ትላላችሁ፡፡ በአሁኑ መግለጫችሁ ደግሞ የኢሳይያስ መንግሥት የአገሪቱን ኅልውና አደጋ ላይ ጥሎታል ብላችኋል፡፡ የኤርትራ ተቃዋሚዎች ከኢሳይያስ የበለጠ የአገሪቱ አንድነትና ኅልውና የመጠበቅ አቅምና ቁርጠኝነት አላቸው?

አቶ ኅሩይ፡-
በመጀመሪያ አንተ የጠቀስከው "ትልቁ ዘፈን" የኢሳይያስ መንግሥት ሊወድቅ ተቃርቧል የሚል ነው፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ የኢሳይያስ ፣ዲክታቶርያል፣ መንግሥት እንዲያውም ኃይለኛና የማይነቃነቅ የሆነበት ነው፡፡ ሕዝቡ ተርቧል ሲባል ይራባ፣ ሕዝቡ ተሰደደ ሲባል ይሰደዳ እያለ፣ "የእኔ ኃላፊነት ይቺ ያለችው ኤርትራ ይዤ መቀጠል ብቻ ነው፣ ለማልቀስ የሚፈልግ ካለ ሌሎች እንደሚያደርጉት ውጭ አገር ሄዶ ዋይ ዋይ ይበል" ነው የእሱ አቋም፡፡ የእኛ አቋም፣ በተለይ በአሁኑ ስብሰባ ተናግረናል፡፡ እባካችሁ "የኢሳይያስ መንግሥት ሊወድቅ ተቃርቧል" የሚል ዘፈን ቢቀር ይሻላል የሚለው ሃሳብ ሁሉም የተቀበለው ይመስላል፡፡ በእርግጥ የተጠናከረው ዱላውን ነው፤ የማይችል አገሩን ለቆ እየሄደ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታዲያ፣ የሕዝቡ መሰደድ ብቻ ሳይሆን የኤርትራ ወታደሮችም እየኮበለሉ ባሉበት ሁኔታ የኢሳይያስ መንግሥት የበለጠ ተጠናክሯል ማለት እንችላለን?

አቶ ኅሩይ፡-
የሚፈለገው እሱ አይደለም እንዴ? የሚሄደው መሣሪያውን ጥሎ ነው እንጂ መሣሪያውን ይዞ ከስደተኞች ጋር ቢተሳሰር ኖሮማ የእሱ መንግሥት ሊወድቅ ይችላል የሚል ግምት እውነተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ድንበሩን ተሻግሮ እንዴት አድርጌ ኑሮዬን ላሻሽል እችላለሁ ነው ሃሳቡ፡፡ ኢሳያስ ጨቁኖ የሚይዝበት ዱላው በጣም አጠናክሯል ማለት ነው፡፡ ከእሱ ጋር ያሉት ጀኔራሎች ደግሞ ለጥቅማቸው ይሁን በሌላ ምክንያት ፈፅሞ አይጠይቁም፡፡

ሪፖርተር፡- ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የተጠናከረ እና በቀላሉ የማይፈርስ ነው ካላችሁት ይህንን ኃይል የሚመጣጠን አዲስ ስትራቴጂ ለምን አላወጣችሁም?

አቶ ኅሩይ፡-
"የስደት መንግሥት" የሚባለውን ሃሳብ በደንብ ከተሠራበት መጀመሪያ የውጭ አገር መንግሥታት ይቀበሉት እና የዲፕሎማሲ እውቅና ያገኛል፡፡ በመሆኑም የተለያዩ ድጋፍ ሊያደርጉለት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አገር ውስጥ ያለው ኤርትራዊ ጥሩ የስደት መንግሥት አለን፣ እኛም ማኅበራዊ አብዮት ልንጀምር እንችላለን ብሎ የመታገል መንፈስ ሊፈጥርለት ይችላል፡፡ አሁን የሚደረገው ኮንፍረንስ "የስደት መንግሥት" ለመፍጠር የማይችል ከሆነ ያው የተለመደው ዓይነት ግንባር የሚባለው ይሆናል፡፡ እሱ ደግሞ የሚያመጣው ለውጥ የለም የሚሉ ናቸው አብዛኛዎቹ፡፡

ሪፖርተር፡- ነገር ግን ተቃዋሚዎች በአንድ ጃንጥላ (ኪዳን) ሥር ቢንቀሳቀሱም ወደ የጋራ መድረክ መሰባሰብ አልቻሉም፣ የተበታተኑ ናቸው፡፡ የስደት መንግሥትን ለመፍጠር የሚያስችል የጋራ ማዕቀፍ ይኖራቸዋል?

አቶ ኅሩይ፡-
ቅድም እንዳልኩህ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በኮንፍረንስ ተሳታፊ ከሆኑ የጋራ ሸንጎ ወይም ጉባኤ መፍጠር ይችላሉ፡፡ ይሄ ማለት ከኪዳን ጋር አብሮ የሚሠራ አዲስ ኃይል መጥቷል ማለት ነው፡፡ ኪዳንና ሕዝብ ተዋህደዋል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መንግሥት ሲፈጠር ካቢኔም ይፈጠራል፡፡ ካቢኔው የተጠቀሱት ወገኖችና ፓርቲዎች ውክልና ይኖረዋል፡፡ የፓርቲ መሪዎች የግድ የካቢኔው መሪዎች ይሆናሉ ማለት አይደለም፡፡ በዚህ አገባብ "አዋቂዎች" የመንግሥቱን መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ግጭት ላይ ጥናቶች ያቀርባሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ ነገር አለ?

አቶ ኅሩይ፡-
አንዳንድ መሻሻሎች ያሉ ይመስላሉ፡፡ በአምባገነኑ የአሥመራ መንግሥትም ይሁን በኢትዮጵያ መሪዎች ላይ የተጣለ ነገር ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ፍ/ቤቱ እኔ ጨርሼያለሁ እናንተ የቤት ሥራችሁን አላጠናቀቃችሁም፡፡ ስትፈለጉኝ ግን ጥሩኝ ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር የቀረበ ባለ አምስት ነጥቦች የመፍትሄ ሃሳብ ነበረ፡፡ ቁጭ ብለን እንነጋገር ነው ያሉት፡፡ አሁንም ቁጭ ብለው ካልተነጋገሩ የድንበሩ ግጭት ሊፈታ አይችልም፡፡ አሁን ግን የኤርትራው አምባገነን የገባው ይመስላል፡፡ ብዙ ጊዜ የአሰብን ጉዳይ ያነሳል፡፡ ቁጭ ብለን እንነጋገር የሚል መንፈስም አለ፡፡ እነዚህ ምልክቶች ይታያሉ፡፡ የምዕራብ ጋዜጦች ያንበብክ እንደሆነ የተለያዩ ተፅዕኖዎች ላይ እንዳለ ታያለህ፡፡ መጥፎ ሰው እንደሆነ እኮ እናውቃለን ግን በእሱ የሚፈቱ ጥያቄዎች አሉ ይላሉ፡፡ ስለ ሶማሊያ፣ ዳርፉር በእሱ መጠቀም የግድ ነው፡፡ እባካችሁን የድንበሩ ጉዳዩ እዩልኝ ይላል፡፡ መጀመሪያ ቁጭ ብለህ ተደራደር ይሉታል፡፡ ከዚያ በኋላ ዓለም አቀፈ ማኅበረሰብ በጉዳዩ ላይ ለመግባት ፍላጎት ሊኖረው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ይሄ የምዕራባውያን ተፅዕኖ እኮ የቆየ ነው፡፡ አዲስ ምልክቶች አሉ ያሉኝ ግን ግልፅ አይደለም፤

አቶ ኅሩይ፡-
አሁን መውጪያ አጣ፡፡ መውጪያውን ደግሞ መፈለግ አለበት፡፡ እንደ ድሮ ባለበት መቀጠል አይችልም፡፡ ከኦባማ አስተዳደር ጋር ታርቄ ምን ማድረግ እችላለሁ የሚል ሙከራ እያካሄደ ነው፡፡ ደብዳቤዎችን ይፅፋል፤ በስቴት ዲፓርትመንቱ በኩል ለመታረቅ ዝግጁ እንዳሆነ እያሳየ ነው፡፡ አሜሪካንን መሳደብ አቁሟል፡፡

ሪፖርተር፡- የፀጥታው ምክር ቤት በሶማሊያ ጣልቃ በመግባቱ ምክንያት በኤርትራ መንግሥት ላይ ማዕቀብ ለመጣል እየዛተ ነው፡፡ ይህ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ በኤርትራ እና በቀጣናው ምን ዓይነት እንደምታ ይኖራል?

አቶ ኅሩይ፡-
የማዕቀቡ ጥያቄ እንዲሁ ችላ የሚባል አይደለም፡፡ ሰውዬውን ከእኛ ጋር መግባባት ከፈለገ እኛም ከእሱ ጋር የማንግባባበት ምክንያት የለም፣ በመግባባት ነው ተፅዕኖ ማሳደር የምንችለው፡ የሚል በምዕራባውያን በኩል አለ፡፡ በአንድ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር ቁጭ ብለህ ተነጋገር የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም የሶማሊያው ችግር መነሻው ይሄ ነው፡፡ የድንበሩ ግጭት ሲፈታ ሌላውም ይፈታል፡፡ በቀጣናው ያለው ትልቁ ግጭት እሱ ነው፡፡ ኢሳይያስ በሶማሊያ ጣልቃ የሚገባው ኢትዮጵያን ለማዳከም ነው፡፡ አስቸጋሪ ሰው ቢሆንም፣ ድሮም እገዛ የሚያደርጉለት ስለነበረ፣ ከእጃቸው እንዲወጣ አይፈልጉም፡፡ ዋናው መፍትሄው በሁለቱም መንግሥት መልካም ፍቃድ የሚደረግ ነው፡፡ ምክንያቱም የግጭቱ መነሻ ባድመ (መሬት) ብቻ አይደለም፡፡ የጦርነቱ አነሳስ እንዴት ነው? የሚለው የመጀመሪያ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ የድንበሩ ግጭት ከተፈታ በኋላ ለመሆኑ እንዴት ነው የምንኖረው? የሚል ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ነገሮችን ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በኋላ የድንበሩ ጉዳይ ቴክኒካልነው የሚሆነው፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ችግር የለበትም፡፡ አንዳንድ መታረም ያለባቸው ግን መነሳታቸው አይቀርም፡፡ እነዚህ በፍ/ቤቱ ውሳኔ ሳይሆን፣ በውል እና በድርድር ነው የሚፈቱት፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በኢትዮጵያ ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት አሰብን በተመለከተ በተቃዋሚዎችና በአንዳንድ ወገኖች እየተወቀሰ ነው፡፡ ይሄ የድርድሩ አካል መሆን ይችላል?

አቶ ኅሩይ፡-
የአሰብ ጉዳይ የድርድር ጥያቄ አይደለም፡፡ የስምምነት ጉዳይ ነው፡፡ የሁለቱም መንግሥታት እና የብሄረ አፋር መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም የአፋር ሕዝብ ጥቅም ተሻግሮ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መንግሥታት መካከል የሚደረግ ስምምነት አይኖርም፡፡ አይቻልምም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት አሰብን በኃይል አለመውሰዳቸው ግን ምን ያህል የሕግ አክባሪዎች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን ከሃዲ ነው የሚሉ ሰዎች ነገሩን አጥብበው በስሜት የተመለከቱት ይመስለኛል፡፡   

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ዋነኛ ተቃዋሚዎች አሰብ የኢትዮጵያ አካል ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ የድርድር ጉዳይ አይሆንም ካሉኝ፣ እነዚህ ኃይሎች ምርጫውን ቢያሸንፉ ጉዳዩ ወደ ጦርነት አያመራም?

አቶ ኅሩይ፡-
ለዚህ እኮ ነው የስምምነት ጉዳይ ነው ያልኩት፡፡ ይሄ ማለት የጥቅም መለኪያዎች ሁሉ ተነስተው ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን እንደዚሁም የአፋር ሕዝብ አብረው መወያየት አለባቸው ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኤርትራ ውስጥ አንዳንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚዎች እየተንቀሳቀሱ ነው፤ እዚህም እናንተ እየተንቀሳቀሳችሁ ነው፡፡ ትርጉሙ ምንድን ነው?

አቶ ኅሩይ፡-
እዚህ ያሉት የኤርትራ ተቃዋሚዎች የሚያነሱት የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እነሱም እኮ የዴሞክራሲ ጥያቄ የሚያነሱ ናቸው፤

አቶ ኅሩይ፡-
ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ፓርቲዎች ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱበት ሕገ መንግሥት ተቀምጧል፡፡ እኛጋ ግን የተፃፈው (እሱም ያልተሟላ) ሕገ መንግሥት ኮመዲና ውስጥ የተቆለፈ ነው፡፡ አሥመራ ያሉት ተቃዋሚዎች ግን እውነት በዴሞክራሲ የሚያምኑ ከሆነ (ምንም ጉድለቶች ቢኖሩም) እዚህ ሆነው ራሳቸውን የማደራጀት ዕድል አላቸው፡፡ እኛ ኤርትራ ውስጥ ይሄ ዕድል የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- ለበርካታ ዓመታት ብዙ መስዋዕት ከፍለው የመጡ፣ ሁለቱም የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ድርጅቶች ለሕዝቡ የተጠበቀውን ያህል ዴሞክራሲ አልፈጠሩም የሚሉ ትችቶችም አሉ፤

አቶ ኅሩይ፡-
እርግጥ ነው፡፡ ለምሳሌ ኤርትራ ውስጥ ከ18 ዓመት በኋላ የምናየው ዴሞክራሲ የለም፡፡ አምባገነንነት ነው ያለው፡፡ ታጋዮቹ ሁሉ እስር ቤት ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡ የተገደሉም አሉ፡፡ እንኳን ዴሞክራሲ፣ የዴሞክራሲ ሽታም የለም፡፡ በጀብሃም በኩል ሆነ በሻዕቢያ በኩል ቆንጆ ቆንጆ የዴሞክራሲ ፕሮግራሞች ነበሩን፡፡ ጀብሃ ስልጣን ይዞ ቢሆን ኑሮ የሚሆነውን አናውቅም፡፡ የሻዕቢያ ግን የምናየው ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ለብዙ ዓመታት በንጉሠ ነገሥትነት የተገዛች አገር ናት፡፡ የዴሞክራሲ ጮራ አይተን አናውቅም፡፡ ከዚያም በኋላ ወታደሮቹ ቀይ ቀለም ተቀብተው የዴሞክራሲ ሽታ አላሳዩንም፡፡ አሁን ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራሲ መኖር አለበት ተብሎ ጥረት መደረጉ አንድ ነገር ነው፡፡ ስፋቱ ግን የሕዝቡም የስልጣኔ ጉዳይ ይወስነዋል፡፡ የተቃዋሚ ኃይሎችም ኃላፊነት ነው፡፡ ራሳቸው ዴሞክራሲያውያን ሆነው፣ እኛ የምናየው ዴሞክራሲ እንዲህ ነው ብለው መወዳደር አለባቸው እንጂ እቤትህ ቁጭ ተብሎ ዴሞክራሲ አይመጣም፡፡ ዴሞክራሲ የተሻለ አስተሳሰብና አማራጭ የማምጣትና የመደራደርም ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መካከል አንዳንዴ መደራደር አለ፡፡ ዴሞክራሲ የድርድር ውጤት ነው ካልን፣ የኤርትራ ተቃዋሚዎችስ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለመደራደር ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ?

አቶ ኅሩይ፡-
ኢሳይያስ እስከ አሁን የሚለው ተቃዋሚዎች አሉ ሲባል "የምን ተቃዋሚዎች?" ነው፡፡ እውቅና ካማይሰጥህ አካል ጋር መደራደር አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ሰው ብቻውን ዴሞክራሲያዊም አምባገነንም ሊሆን አይችልም፡፡ የባህል ቢያንስ ደግሞ የሊኒቃኑ መገለጫ ነው፡፡ ኤርትራ ውስጥ ኢሳይያስ ብቻውን ነው አምባገነን ወይስ".?

አቶ ኅሩይ፡-
አሁን ያለው አምባገነንነት በትጥቅ ትግል ጊዜ የታነፀ ነው የሚመስለኝ፡፡ ያኔ ይመሩ የነበሩ አሁንም ስልጣን ላይ ያሉ ናቸው፡፡ እርግጥ ከመካከላቸው አብዛኛዎቹ ታስረዋል፡፡ አንዳንዶቹም ሞተዋል፡፡ የተቀሩት ግን በርሃም ከኢሳይያስ ሆነው መሪዎች የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን ኢሳይያስ ዴሞክራት ቢሆን ኖሮ እነሱም ዴሞክራት ይሆኑ ነበር ማለቴ ነው፡፡ አምባገነንነቱ ከላይ የተፈጠረ ነው፤ የሕዝቡ ባህል ወይም አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ዴሞክራሲን የሚያሰፋ ሕገመንግሥትና ምርጫ ነው፡፡ እሱም ደግሞ ተዘጋ፡፡ ክፍት ቢሆን እና ምርጫ ቢደረግ የዴሞክራሲ መስኮቶች ይከፈቱ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የኤርትራ ተቃዋሚዎች ዓላማ ኢሳይያስን አስወግዳችሁ ስልጣን መያዝ ነው፡፡ በሆነ ምክንያት በውጭ ሃይል እንዲወገድላችሁ ትፈልጋላችሁ?

አቶ ኅሩይ፡-
መጀመሪያ የውጭ መንግሥት የኤርትራን አምባገነን ለመጣል ከፈለገ በራሱ ምክንያት ነው እንጂ በእኛ ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ የእኛ ጥያቄዎች የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ሁለተኛ፣ አምባገነኑ በውጊያ የወደቀ እንደሆነ ግን እኛ ተቃዋሚዎች የአገራችን ጉዳይ ራሳችን እንመራዋለን ማለታችን አይቀርም፡፡ የውጊያው ውጤት አምባገነኑን ከጣለ የተቀረውን እኛ ነን የምንመራው ማለቴ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕዝብ ባይቀበላችሁስ?

አቶ ኅሩይ፡-
እኛን ያልተቀበለን እንደሆነ ደግሞ የራሱ መንግሥት ይተክላል፡፡
 
Copyright © 2018 Eritrean Congress Party Strategy Adi. All Rights Reserved.